በአቋራጭ የበለጸጉ የመንግስት አመራሮች የሃብት ምንጭ ምንድን ነው?

መንግስት ራሴን መፈተሽ ጀምሬአለሁ አለ!!!
200 ገደማ የአማራ ክልል አመራሮች ከሃላፊነት ተባረሩ

ማስተርፕላኑ እንኳንስ በፊንፊኔ ዙሪያ ጂማን ተሻግሮ መላ ጦቢያን ቢያካልል ነፍሴ በሃሴት ጮቤ ትረግጥ ነበር፡፡ ዋናው ነገር ግን የእኔ ደስታ ወይም ፍላጎት አይደለም፡፡ (የኦህዴድና የመንግስት ራዕይና ዕቅድም ቦታ የላቸውም!) ከሁሉ የሚቀድመው የኦሮሚያ ህዝብ ፍላጐትና ምርጫ ነው፡፡

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች “ሂዩማን ራይትስ ዎች”፤ በኦሮሚያ ክልል ማስተርፕላኑን መነሻ አድርጐ በተቀሰቀሰው ተቃውሞና እሱን ተከትሎ በተከሰተው ግጭት 140 ሰዎች መሞታቸውን አስታውቋል፡፡ (አሳዛኝ የታሪካችን አካል ነው!) መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው “ሂዩማን ራይትስ ዎች”፤ በኦሮሚያ በተከሰተው ግጭት የሞቱትን ዜጎች ቁጥር ይፋ ካደረገ አንድ ሳምንት አልፎታል። የኢትዮጵያ መንግስት፣ አገር በቀሎቹ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች እንዲሁም የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ግን እስካሁን የሞቱትንና የቆሰሉትን ዜጎች ቁጥር አልነገሩንም፡፡ (መንግስት የመንገር ሃላፊነት፣ እኛ የማወቅ መብት ያለን መስሎኝ!?) ለነገሩ የክልሉ መንግስት፤ የደረሰውን ጉዳት በጥንቃቄ እያጣራ መሆኑን ጠቁሞ፣ ማጣራቱ እንደተጠናቀቀም ለህዝብ ይፋ አደርጋለሁ ብሎ ነበር፡፡ (ዝንተ ዓለም ፈጀ እኮ!)
የሚያሳዝነው ደግሞ ነገርዬው በዚህ አለመቋጨቱ ነው፡፡ በሁካታውና ዕልቂቱ ማግስት ረብሻውን ቀስቅሰዋል ተብለው የተጠረጠሩ፣ የተጠቆሙ፣ የተጋለጡ …ብዙ ሺዎች — ወህኒ ወርደዋል ተብሏል። ግን ስንት ሺዎች? ለመሆኑ ከጅምሩ እስካሁን ድረስ ምን ያህል ሰዎች ተጠርጥረው ተያዙ? ምን ያህሎቹ ፍ/ቤት ቀረቡ? ስንቶቹስ በነፃ ተለቀቁ? ህዝባዊ መንግስታችን ይሄን መረጃ የሚነግረን መቼ ነው? ይሄም እየተጣራ ይሆን? (ግን እኮ የታሰሩትን ዝም ብሎ መቁጠር ነው!) አለዚያ ግን ብቸኛው አማራጫችን መቀመጫቸውን በአሜሪካ ያደረጉት እነ አምነስቲ ኢንተርናሽናል እንደተለመደው ሪፖርት እስኪያወጡ መጠበቅ ነው። (ከኒዮሊበራሊዝም አቀንቃኞች ነጻ የምንወጣው መቼ ነው?)
በእስከዛሬው ልምዳችን መሰረት፣ እነ ሂዩማን ራይትስዎች ወይም ፍሪደም ሃውስ አሊያም ዊዝአውት ቦርደርስ —-በኦሮሚያ በተከሰተው ፖለቲካዊ ቀውስ ሳቢያ ለእስር የተዳረጉትን ዜጎች ቁጥር ከማንም በፊት ቀድመው ይነግሩናል። በእርግጥ የቁጥር ከፍና ዝቅ ሊኖር ይችላል፡፡ አሜሪካ ሆነው እቅጭዋን ሊነግሩን አይችሉም፡፡ (እቅጭዋን የሚያውቀውማ አሳሪው ነው!) አንድ ነገር ትዝ አለኝ፡፡ በዕድለ ቢሱ የ97 ምርጫ ሰሞን የተከሰተ ነው፡፡ የምርጫ ውጤት ተጭበርብሯል የተባለ ሰሞን ታክሲዎች አድመው ነበር፡፡ ለ3 ቀናት ገደማ ሳይሆን አይቀርም፡፡ በ4ኛው ቀን ላይ ሚኒባስ ታክሲዎች አገልግሎት መስጠት ጀመሩ፡፡ አዲስ አበባ ከድብርቷና ከኦናነቷ ተላቃ ወደ ቀድሞው ድባብ የመመለስ ፍንጭ አሳየች፡፡ የዚያን ላይ ማታ የድሮው ኢቲቪ ያስተላለፈው ዘገባ መቼም አይረሳኝም፡፡ (ሃሳቡን እንጂ ቃል በቃል ትዝ አይለኝም!) “በዛሬው ዕለት የአዲስ አበባ ሚኒባስ ታክሲዎች አገልግሎት ሲሰጡ መዋላቸውን ሮይተርስ ዘገበ” (ለሸገር የሚቀርባት ሮይተርስ ነው ኢቲቪ?)
በነገራችን ላይ በኦሮሚያ በተከሰተው ረብሻና ግጭት እንዲሁም ዕልቂት አንድ አሳዛኝ እውነታ ተገንዝቤአለሁ፡፡ (ታዝቤአለሁ ማለት ይቀለኛል!) ለሳምንታት በዘለቀው ግጭት የመንግስት የፀጥታ ኃይል ለተቃውሞ በወጡ ዜጎች ላይ ያልተመጣጠነ እርምጃ ከመውሰድ እንዲቆጠብ ያሳሰቡት ውቅያኖስ ማዶ ያሉት የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ብቻ ናቸው፡፡ (ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ውጭ ማለቴ ነው!) በመንግስት የተቋቋመው “ኢሰመኮ” እና በፕ/ር መስፍን  የተቆረቀረው “ሰመጉ” ትንፍሽ ያሉት ነገር የለም፡፡ (የሰብአዊ መብት ተቋማት መስለውኝ?!) ወዳጆቼ፤ በዚያ ቀውጢ ሰዓት መንግስትን ለምን አላወገዙም ወይም አልተቃወሙም እያልኩ አይደለም፡፡ መንግስት አቅሉን ስቶ ግብታዊ ነገር እንዳይፈጽም የምታሳስብ፣ የምታስታውስ መግለጫ ቢጤ ማውጣት ማን ገደለ? ሌላው ቢቀር እንደ እነ አሜሪካ ኤምባሲ፤ “የሞቱት ዜጐች…የታሰሩት ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች ጉዳይ ያሳስበኛል” ማለት እንዴት ያቅታል?! ይሄን በማድረጋቸው መንግስት የሚያስራቸው ከመሰላቸው ከ25 ዓመት በፊት ወደነበረው ሥርዓት ተመልሰናል ማለት ነው፡፡
ሌላው ሁሌም እዚህ አገር የማይገባኝ ምን መሰላችሁ?… የሃይማኖት ተቋማትና መሪዎች (አባቶች) ሚና ነው? በአማራ ክልል በሉት በኦሮሚያ ያ ሁሉ ሁከትና ግጭት ሲከሰት …ዜጐች ሲሞቱ —- ተቋማቱ የት ነበሩ? ያንዳቸውም ድምጽ አልተሰማም፡፡ (ፖለቲካና ሃይማኖትን መቀላቀል ስለማይፈቀድ ይሆን?) ለነገሩ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሃይማኖት መሪዎች በየበዓሉ የሚሰጡትን መግለጫ ከተከታተላችሁልኝ —– እያደር አንደበታቸው የፖለቲከኛ እየመሰለ መጥቷል። አንዳንዶቹማ የካድሬ ቋንቋ ሁሉ ለምደዋል፡፡ ግና—- ሰላምና ፍቅርን፣ መከባበርና መቻቻልን… መስበክ አልቻሉም፡፡ እርቅ ማውረድ ተስኗቸዋል። ህዝብን —– ከህዝብ፣ ህዝብን —— ከመንግስት —– መምከር፣ ማስማማት፣ ማስታረቅ አቅቷቸዋል።   ከእግዚአብሄር ይልቅ መንግስትን ይፈራሉ፡፡ ከሰማያዊው ዓለም ምድራዊው ግምኛ ያጓጓቸዋል፡፡
በእርግጥ መንግስት እንዳይጠምዳቸው ሰግተው ይሆናል፡፡ ነገር ግን ይሄ መሰረተ – ቢስ ስጋት ነው፡፡ ይልቁንም የእነሱ አስተዋጽኦ መንግስትን አማራጭ አጥቶ ወደ ሃይል እርምጃ ከመግባት ሊያድነው ሁሉ ይችል ነበር፡፡ ችግሩ ግን እነሱ ከኛ ከተራ ተርታዎቹ ምድራዊ ሰዎች እንኳን ብሰዋል፡፡ ይሄን በማድረግ ዓለማዊው ምቾታቸውን እንዲቀንሱ አይሹም፡፡ የሆኖ ሆኖ እኛ አዝነንባቸውና ታዝበናቸው አልፈናል። እንግዲህ በውስጤ ሲብሰለሰል የሰነበተውን ቅሬታና ቁጭታ፣ እቺን ታህል ከተነፈስኩ ይበቃኛል፡፡ (ክብር ለህገ-መንግስቱ!)
ይህ በዚህ እንዳለ ባለፈው ማክሰኞ ማታ፣ ከኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ያልተጠበቀ መግለጫ ወጥቷል (በኢቢሲ ማለቴ ነው!) በግሌ ደስ ነው ያለኝ፡፡ “ለጋራ ልማት የታሰበው የአዲስ አበባና ፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ የጋራ ልማት ሙሉ ለሙሉ እንዲቆም የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ውሳኔ አስተላለፈ” ይላል የኢቢሲ ዜና፡፡ ሌሎች ቅሬታዎችና ጥያቄዎች ቢኖሩም ዋናው የኦሮሚያ ክልል ተቃውሞ መነሻ፣ ይሄው ማስተርፕላኑ ነው። እናም ውሳኔው ተገቢ ይመስለኛል፡፡ (ልማት ተግባብቶ እንጂ ተለያይቶ የለም!) በነገራችን ላይ እኔ በግሌ ማስተርፕላኑ ቢተገበር ደስታውን አልችለውም፡፡ እንኳንስ ልማት ሌላውም ሁሉ በክልል፤ በጐሳ፣ ወዘተ —– ባይገደብ እመርጣለሁ። እናም ማስተርፕላኑ እንኳንስ በፊንፊኔ ዙሪያ ጂማን ተሻግሮ መላ ጦቢያን ቢያካልል ነፍሴ በሃሴት ጮቤ ትረግጥ ነበር፡፡ ዋናው ነገር ግን የእኔ ደስታ ወይም ፍላጎት አይደለም፡፡ (የኦህዴድና የመንግስት ራዕይና ዕቅድም ቦታ የላቸውም!) ከሁሉ የሚቀድመው የኦሮሚያ ህዝብ ፍላጐትና ምርጫ ነው፡፡ ለዚህ ነው መግለጫው ደስ ያለኝ፡፡ (መዘግየቱ ቢያበሳጨኝም!)
ኢቢሲ በድረገፁ ላይ ባወጣው ዘገባ እንዲህ ሲል ይቀጥላል፤ “ኦህዴድ በልማት፣ በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ከህዝቡ ጋር በመሆን መጠነ ሰፊ ስራዎችን በማከናወን ህዝባዊነቱን ያረጋገጠ ድርጅት መሆኑን ማዕከላዊ ኮሚቴው ገልጿል” (ዜና ነው ፕሮፓጋንዳ?) ቀጣዩ አንቀፅ ሳይሻል አይቀርም። እንዲህ ይላል፡- “በክልሉ የጋራ ፕላኑን መነሻ በማድረግ ህዝቡ የግልፅነት ጥያቄ መጠየቁ ድርጅቱ እየገነባ ያለው ሥርዓት ውጤት በመሆኑ፣ በታላቅ አክብሮት ይመለከተዋል”  (እኛም የኦህዴድን መግለጫ በታላቅ አክብሮት እንመለከተዋለን – የህዝብ ውጤት በመሆኑ!)
የኦህዴድ መግለጫ በዚህ ብቻ አያበቃም፡፡ ክልሉ ከአዲስ አበባ ማግኘት ባለበት ጥቅም ዙሪያ በህገ መንግስቱ በተቀመጠው አቅጣጫ፣ በአጭር ጊዜ ምላሽ እንደሚሰጠውም አስታውቋል፡፡ (የእስከ ዛሬውን ዳተኝነት በምን ፍጥነት ያካክሰው ይሆን?)
ኢቢሲ ዘገባውን ሲቀጥልም፤ “የክልሉ ከተሞችን ልማት ለማፋጠን በጨፌ ኦሮሚያ በፀደቀው የከተሞች ልማት አዋጅ አንዳንድ አንቀፆች ዙሪያም ህዝቡ ያነሳቸውን የግልፅነት ጥያቄዎች ለመመለስ የክልሉ መንግስት አዋጁ እንደገና በጨፌ እንዲታይ እንዲያደርግ ድርጅቱ ውሳኔ አስተላልፏል” ብሏል። (“የቸገረው እርጉዝ ያገባል” እንዳይሆን እንጂ አስገራሚ ለውጥ ነው!!) በነገራችን ላይ ኦህዴድ … ትንሽ በጥሞና ቢያስብ ኖሮ ዛሬ የወሰዳቸውን እርምጃዎችም ሆነ ያስተላለፋቸውን ውሳኔዎች ቀውስ ከመፈጠሩ ቀደም ብሎ ሊያደርጋቸው ይችል ነበር፡፡ (አገር በተቃውሞ እስክትናጥ መጠበቅ ዋጋ ያስከፍላል!!)
አሁን ደግሞ ወደ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን “ጮማ” የሆነ ወሬ ልምራችሁ፡፡ “በአቋራጭ የበለፀጉ የመንግስት አመራሮችን የሀብት ምንጭ የመፈተሽ ሥራ ተጀምሯል” ይላል ዜናው፡፡ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የኢኮኖሚና የፋይናንስ ክላስተር አስተባባሪና የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ለፋና እንደገለፁት፤ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ መንግስት ከአመራሩና ኃላፊዎቹ ጀምሮ ራሱን መፈተሽ ጀምሯል (“ጉድ ፈላ አትሉኝም!)
በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ልዩ ትኩረት የተሰጠው የመልካም አስተዳደር ችግር ምንም እንኳን በአንድ ሌሊት የሚፈታ ባይሆንም ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ የተግባር እንቅስቃሴዎች በየደረጃው መጀመራቸውን የገለፁት ሚኒስትሩ፤ “ለዚህም በራሳቸውና በቤተሰቦቻቸው ያለ አግባብ ሀብት ያካበቱ የመንግስት አመራሮችን የመፈተሽ ሥራ መጀመሩን ለአብነት አንስተዋል” ሲል ዘግቧል ፋና፡፡ (ይሄኔ ነው እንግዲህ “እናቴ፤ ምነው በእንቁላሉ ጊዜ በቀጣሽኝ” የሚለው የሚበዛው!) አንዳንዴ እኮ እናት በደንብ ቆንጥጣ ብታሳድገውም ፓርቲና ሥልጣን የሚያበላሸው ሞልቷል (በእናት መፍረድ አይገባም ለማለት ነው!)
ዜናው አልተቋጨም…“ይህን እንቅስቃሴ መንግስት ጥቆማ ሳይጠብቅ የሚሰራው ስራ ሲሆን ችግሩን ለመቅረፍ ግን የህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ ነው” ብለዋል – ሚኒስትሩ፡፡ መንግስት እንደ ሌላው ነገሩ ሁሉ እዚህም ላይ ዘገየ እንጂ የሚደገፍ እርምጃ ነው፡፡ (ሌላው ቢቀር አዳዲስ “የመንግስት ሌቦች”ን ተስፋ ያስቆርጣል!)
እኔ የምለው ግን … በአቋራጭ የበለፀጉ የመንግስት አመራሮች የሀብት ምንጭ ምን ይመስላችኋል? ሀ) ዓለም ባንክ ለ) ኪራይ ሰብሳቢ ባለሀብት ሐ) ደላላ መ) የመንግስት ካዝና ሠ) ከሀ በስተቀር ሁሉም መልስ ናቸው
(ስፖንሰር አድራጊ ባለማግኘቴ ሽልማት የለውም!)
አሁን ደግሞ ወደ አማራ ክልል ላሻግራችሁ። እዚያ የምናገኘው ደግሞ ከመልካም አስተዳደር ጋር ተያይዞ ችግር ፈጥረዋል የተባሉ ከ190 በላይ አመራሮችና ሰራተኞች ከኃላፊነታቸው መነሳታቸውን የሚዘግብ ዜና ነው፡፡ ለመሆኑ ከመልካም አስተዳደር ጋር የተያያዘ ችግር … ሲባል ምን ማለት ነው? (አብስትራክት አልሆነባችሁም?!) ዘገባውን ስታነቡ ግን ምን ዓይነት ትራጄዲ እንደሆነ ትገነዘባላችሁ፡፡ እንዲህ ይላል፡- “… ለድርቅ ተጎጂዎች እንዲደርስ የታሰበውን ድጋፍ ለግል ጥቅማቸው በማዋል ችግር የፈጠሩ (ችግር የፈጠሩ ሳይሆን ከተራበ  ወገን ላይ የነጠቁ!) 90 አመራሮች ከኃላፊነታቸው ተነስተው ጉዳያቸው በህግ እንዲያዝ ተደርጓል” (ይሄማ በጦር ፍርድ ቤት ነው መታየት የነበረበት!)
የፋና ዘገባ እንደሚጠቁመው፤ ሌሎች 6 የዞን አመራሮች ደግሞ ከህብረተሰቡ ለልማት የተሰበሰበ ገንዘብን ለግል ጥቅማቸው በማዋላቸው (ያፈጠጠ ያገጠጠ ምዝበራ በሉት!) ከኃላፊነት ተነስተዋል ተብሏል፡፡ (ለልማት እያሉ ህዝቡን ሲገፉት ኖረዋላ?!) ፍትህ ለህብረተሰቡ ያሰፍናሉ ተብለው የሚታመኑት ዳኞችም በአማራ ክልል “ከደሙ ንፁህ ነኝ” ለማለት አልቻሉም፡፡ (ሁሉም ባይሆኑም!) እናላችሁ…በዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ህብረተሰቡን ሲያጉላሉ የነበሩ የሁለት ዳኞችን ጉዳይ በማጣራት ከኃላፊነት እንዲነሱ ታዟል፡፡
የአማራ ክልል የመልካም አስተዳደር “ጉድ”፤ በዚህ ብቻ የሚያበቃ እንዳይመስላችሁ፡፡ ፖሊሶችንም አነካክቷል፡፡ እጅ መንሻ (ተሽሞንሙኖ ነው እንጂ “ጉቦ” እኮ ነው!) የሚጠይቁና ህዝቡን በማጉላላት የባለጉዳዩን መብት ተጋፍተዋል የተባሉ 45 የፖሊስ አካላት፤ ትጥቃቸውን እንዲፈቱ መደረጋቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ ሌሎች 32 የቀበሌ አመራሮች በፈጠሩት የመልካም አስተዳደር ችግር ከኃላፊነታቸው ተነስተው ጉዳያቸው በህግ እየታየ መሆኑን አመልክቷል፡፡ “የመልካም አስተዳደር ችግር የፈጠሩ…” የሚለው ከወንጀሉ ድርጊት ጋር ስለማይመጣጠን ተመጣጣኝ ቃል ይፈለግለት፡፡ መልካም ሰንበት!

በ ኤልያስ

ከ አዲስ አድማስ ጋዜጣ

 

Advertisements

“ከአገዛዝ ወደ ነፃነት የምንሸጋገርበት ትግል ላይ ነን” ኢ/ር ይልቃል ጌትነት፤ የሰማያዊ ፓርቲ ሊ/መንበር

ይልቃል ጌትነትየሰማያዊና ኦፌኮ ፓርቲ አባላትና አመራሮች መታሰራቸውን ሰማያዊ ፓርቲ ያወገዘ ሲሆን፤ “አሁን የፓርቲ ፖለቲካ የምናደርግበት ጊዜ ላይ አይደለንም፤ ከአገዛዝ ወደ ነፃነት የምንሸጋገርበት ትግል ላይ ነን” ብለዋል የፓርቲው ሊ/መንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት፡፡
የሰማያዊ አመራሮች ባለፈው ረቡዕ በፅ/ቤታቸው በሰጡት መግለጫ፤ በኦሮሚያ ክልል የተፈጠረውን ተቃውሞ ተከትሎ ዜጎች መገደላቸውንና በርካቶች መታሰራቸውን በመጥቀስ “መንግስት ፋና ወጊ የሆኑትን ተራ በተራ እየለቀመ የእሳት እራት እያደረጋቸው ነው” ሲሉ ወቅሰዋል፡፡
የፓርቲው ልሳን የሆነው የ“ነገረ ኢትዮጵያ” ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ፣ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው፣ የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የነበረው ዮናታን ተስፋዬ፣ የፓርቲው አባላት፡- ቴዎድሮስ አስፋው፣ ዳንኤል ተስፋዬ፣ ኤርሚያስ ፀጋዬና ፍሬው ተክሌ መታሰራቸውን የጠቆመው ሰማያዊ፤ የታሰሩት አባላት ፍ/ቤት ቀርበው፣ ፖሊስ በሽብር ወንጀል እንደጠረጠራቸው በመግለፅ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ ጠይቆባቸዋል ብሏል፡፡
በቅርቡ ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ በኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር ዙሪያ ለፓርላማ ያደረጉትን ንግግር የተቹት የፓርቲው ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል፤ “ጠ/ሚኒስትሩ  ለፓርላማ ባደረጉት ንግግር፤ ኢትዮጵያውያን የሱዳንን ድንበር የደፈሩ አስመስለው ዜጎችን “ሽፍቶች” በማለት የማይረሳ ታሪካዊ የክህደት ምስክርነት ሰጥተዋል” ሲል ብለዋል፡፡

በአለማየሁ አንበሴ

ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ

ሰማያዊ ፓርቲ እና መድረክ በጋራ ሰላማዊ ሰልፍ ጠሩ!

11018316_985284501516716_759733404379180901_nሰማያዊ ፓርቲ እና የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) አዲስ አበባ ላይ በጋራ ሰላማዊ ሰልፍ መጥራታቸውን የሰማያዊ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ነገሰ ተፋረደኝ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ እና መድረክ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት መስማማታቸው የሚታወስ ሲሆን እሁድ ታህሳስ 17/2008 ዓ.ም በጋራ ሰልፍ መጥራታቸውን አቶ ነገሰ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡

ሰማያዊ ፓርቲና መድረክ የጠሩት ሰልፍ በዋነኛነት ከማስተር ፕላኑ ጋር በተያያዘ መንግስት እየወሰደው ያለውን እርምጃ፤ እንዲሁም መንግስት ለሱዳን አሳልፎ ለመስጠት ያቀደውን መሬቱ እንዳይሰጥ ለመቃወም ያለመ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሰልፉ ላይ በሰብአዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ላይ መንግስት እየወሰደው ያለውን እፈና እና እርጃዎቸ እንደሚያወግዙ ምክትል ሊቀመንበሩ ተገልፆአል፡፡

ሰማያዊ ፓርቲ እና መድረክ በጋራ የሚያደርጉት ሰልፍ መነሻውን ፒያሳ ራስ መኮንን ድልድይ አድርጎ፣ በቸርቺል አደባባይ የሚያልፍ ሲሆን መዳረሻው ኢትዮ-ኩባ አደባባይ መሆኑን ታውቋል፡፡ መንግስት እየወሰዳቸው ባሉ የተሳሳቱ እርምጃዎች ሀገራችን አጣብቂኝ ውስጥ መሆኗን የገለፁት አቶ ነገሰ ተፋረደኝ ሀገራችን ካለችበት ችግር ለማውጣት ኢትዮጵያውያን በጋራ እንዲቆሙና በሰልፉም እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ሰልፉ እሁድ ታህሳስ 17/2008 ዓ.ም ከጠዋቱ 3 ሰዓት ፒያሳ ራስ መኮንን ድልድይ ላይ እንደሚጀምር ለማወቅ ተችሏል፡፡

መንግሥት ተቃውሞውን ለማርገብ ያልተመጣጠነ ኃይል እንዳይጠቀም እነ አምነስቲ አሳሰቡ!

መንግሥት ተቃውሞውን ለማርገብ ያልተመጣጠነ ኃይል እንዳይጠቀም እነ አምነስቲ አሳሰቡ

ትላንት በአ.አ ዩኒቨርሲቲ ተቃውሞ ተቀሰቀሰ

መንግሥት በኦሮሚያ የተነሳውን መጠነ ሰፊ ተቃውሞ ለማርገብ ያልተመጣጠነ ኃይል ከመጠቀም እንዲቆጠብ አለማቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ያሳሰቡ ሲሆን መንግሥት በበኩሉ፤ ሁኔታው ወደ ለየለት ሥርዓት አልበኝነት መቀየሩን ገልፆ ሁከቱን ለማስቆም የማያዳግም እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል፡፡
መድረክ ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ፤ ተቃውሞውን ተከትሎ በተፈጠረው ግጭት 32 ሰዎች በመንግስት የፀጥታ ኃይሎች መገደላቸውን ያስታወቀ ሲሆን አምነስቲ ኢንተርናሽናል የሟቾች ቁጥር ወደ 40 እንደሚጠጋ ገልጿል። መንግሥት በግጭቱ በርካታ ሰዎች መሞታቸውን ቢያምንም የሟቾች ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ አልጠቀሰም፡፡
አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ሂውማን ራይትስ ዎች ሰሞኑን በጉዳዩ ላይ ባወጡት መግለጫ፤ መንግስት ተቃውሞ በሚያሰሙ አካላት ላይ ያልተመጣጠነ ኃይል ከመጠቀም እንዲቆጠብ ጠይቀዋል፡፡ መንግሥት የዜጎችን ሃሳብን በነፃነት የመግለፅና ሰላማዊ ተቃውሞ የማድረግ መብት ከማክበር ይልቅ ጉዳዩን ከሽብርተኝነት ጋር  ማያያዙ አግባብ አይደለም ብሏል አምነስቲ፡፡
“መንግሥት ተቃውሞ ያሰሙትን ሁሉ በሽብርተኝነት ፈርጇል” ያለው አምነስቲ፤ “ከህግ አግባብ ውጪ በፀጥታ ኃይሎች የሚፈፀምን ግድያ ከማውገዝ ይልቅ ተቃዋሚዎቹን ሽብርተኛና ሀገር ሊበጠብጡ የተነሱ ናቸው ማለቱ አግባብ አይደለም” ሲል ተቃውሟል። የውዝግቡ መነሻ ከሆነው ማስተር ፕላን ጋር በተያያዘ በ2006 ዓ.ም ተመሳሳይ ግጭት ተፈጥሮ የበርካቶች ህይወት ጠፍቶ እንደነበር ያስታወሰው ሂውማን ራይትስ ዎች በበኩሉ፤ ያኔም ሆነ አሁን በተነሳው ተቃውሞ በርካቶች መገደላቸውን፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ መታሰራቸውን አስታውቋል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት በተነሳው ተቃውሞ አብዛኞቹ የተቃውሞው ተሳታፊዎች ተቃውሞ ስላቀረቡ ብቻ ጉዳዩ ከሽብር ተቆጥሮ በሽብር እንደተፈረደባቸው የጠቀሰው ሂውማን ራይትስ ዎች፤ በወቅቱ ታስረው የነበሩ ተማሪዎች በእስር ቤት ውስጥ ግርፋትና ስቃይ ደርሶባቸዋል ብሏል፡፡
ከሦስት ሳምንታት በላይ ለዘለቀው ተቃውሞ መንግሥት የፀጥታ ኃይሎቹ ከመጠን በላይ ኃይል እንዳይጠቀሙ ሊከላከል ይገባ ነበር ያለው የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ፤ ህግ የጣሱ አካላት በገለልተኛ ወገን ተጣርቶ ተገቢውን ቅጣት ማግኘት አለባቸው ብሏል፡፡
መድረክም በበኩሉ፤ በሰላማዊ ዜጎች ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ በአስቸኳይ እንዲቆምና ጉዳት ለደረሰባቸው ቤተሰቦች ካሳ ተከፍሎ ግድያውን የፈፀሙ ወገኖች በህግ እንዲጠየቁ አሳስቧል፡፡ መንግስት በበኩሉ፤ ከማስተር ፕላኑ ጋር ተያይዞ የተነሳው ተቃውሞ ባህርዩን ለውጦ ወደለየለት ሁከት  መቀየሩን ጠቁሞ የታጠቁ ኃይሎች ስርአት እናፈርሳለን እያሉ በመሆኑ አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል፡፡ በእነዚህ ኃይሎች የጥፋት እርምጃም የሞዴል አርሶ አደሮች ማሳ፣ የመንግሥትና የህዝብ እንዲሁም የወረዳና የቀበሌ አመራሮች ቤት ንብረት ወድሟል ያለው መንግሥት፤ የየወረዳዎቹ የመንግሥት አመራሮችና የፀጥታ አካላትም በግልፅ ጥቃት ተከፍቶባቸዋል ብሏል፡፡
የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ በሰጡት መግለጫ፤ በምዕራብና በደቡብ ምዕራብ ሸዋ አካባቢዎች ስርአት አልበኝነት መስፈኑን ጠቁመው አስፓልቶች መቆፈራቸውን፤ ፋብሪካዎችና የገበሬ ማሳዎች ላይም ጥቃት እየተፈፀመባቸው እንደሆነ በመግለፅ መንግስት ይሄን ሁከት ለማስቆም አስፈላጊውን እርምጃ ይወስዳል ብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርም ደሳለኝ በበኩላቸው፤ ተቃውሞው አቅጣጫውን እየቀየረ መሆኑን አስረድተው፤ መንግስታቸው ተከታታይ እርምጃ እንደሚወስድና ሀገሪቱን የማረጋጋት ኃላፊነቱን እንደሚወጣ ተናግረዋል፡፡
ተቃውሞውን ተከትሎ በሶስት የኔዘርላንድ የአበባ እርሻዎች ላይ ጥቃት እንደተሰነዘረባቸውና ሁለቱ ሙሉ ለሙሉ እንደወደሙ በኢትዮጵያ የኔዘርላንድ ኤምባሲ ያስታወቀ ሲሆን ዳንጎቴ ሲሚንቶም የጥቃቱ ሰለባ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ መንግስት በበኩሉ፤ ለነዚህ የልማት ድርጅቶች አስፈላጊውን ጥበቃ በማድረግ ላይ እንደሆነ ገልጿል፡፡  በወንጪ ከተማ የሚገኘው የሶላግሮ ኢንዱስትሪም ፤ ከ28 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት እንደወደመበት አስታውቋል፡፡
ሦስተኛ ሳምንቱን በያዘው ተቃውሞ በምዕራብና በደቡብ ምዕራብ የኦሮሚያ አካባቢዎች በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ግጭቱ ማየሉን መንግስት ያስታወቀ ሲሆን በኢጃጂ፣ በግንደበረት፣ በአምቦ፣ ወሊሶ፣ አርሲ ዶዶላ፣ ሜታ ሮቢ፣ ሙገር፣ ሃረማያ፣ አወዳይ፣ ደምቢዶሎ፣ ዲላላ፣ አይራ ጉሊሶ፣ ነጆ፣ ዪብዶ፣ መቱ፣ ወንጪ፣ ቡራዩና ሱሉልታ በመሳሰሉት አካባቢዎች ሁከቱ መቀጠሉንና በአብዛኞቹ ከተሞችም የፀጥታ ኃይሎችና ተቃዋሚዎች መጋጨታቸውን ገልፆ ነበር፡፡
መንግሥት በሰጠው መግለጫ፤ ግጭቱን ተከትሎ በሰዎች ላይ ከደረሰው ሞት በተጨማሪ ከፍተኛ የንብረት ውድመት የደረሰ ሲሆን ባንኮች፣ የግል ድርጅቶች፣ የእርሻ ማሳዎች፣ የመንግሥት አስተዳደር ፅ/ቤቶች፣ የወረዳና ቀበሌ አመራር መኖሪያ ቤቶች እንዲሁም ፍ/ቤቶች  እንዲቃጠሉ ተደርገዋል፡፡ ከዚህም ሌላ እስረኞች ከማረሚያ ቤት እንዲያመልጡ ተደርጓል ብሏል – መንግሥት፡፡
ተቃውሞው ሲጀምር በተማሪዎች ይሁን እንጂ አርሶ አደሮችና ሰራተኞች በስፋት እንደተቀላቀሉት ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ ግጭቱ ባየለበት የደቡብ ምዕራብና ምዕራብ ኦሮሚያ አንዳንድ ከተሞች ህብረተሰቡ ወደየከተሞቹ የሚያስገቡ አውራ ጎዳናዎችን በድንጋይና በእንጨት በመዘጋጋት፣ የፀጥታ ኃይሎችን እንቅስቃሴ ለመገደብ ጥረት እያደረጉ ሲሆን ከትናንት በስቲያ ከአዲስ አበባ በ20 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምትገኘው ሱሉልታ ከተማ በተነሳው ተቃውሞ ወደ ጎጃም መውጫ መንገድን በመቆፈር እንዲዘጋ መደረጉ ታውቋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትላንትና ጠዋት ተቃውሞ ተነስቶ የነበረ ሲሆን በፌደራል ፖሊስ ሃይል መገታቱን ምንጮች ገለጹ፡፡ ለተቃውሞው መነሻ ነው የተባለው ሃሙስ ሌሊት ፖሊስ 2 ሴት ተማሪዎችን  ከዶርም እያለቀሱ ወዳልታወቀ ቦታ መውሰዱ እንደሆነ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ በነጋታው አርብ ጠዋት ተማሪዎች በሰልፍ ወደ ዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ቢሮ በማምራት፣ሌሊት የተወሰዱት ጓደኞቻችን የት ገቡ ሲሉ ፕሬዚዳንቱን የጠየቁ ሲሆን  አጥጋቢ ምላሽ አለማግኘታቸውን ምንጮች ተናግረዋል፡፡ በዚህ የተናደዱት ተማሪዎች ተቃውሞአቸውን እያሰሙ ከግቢው ለመውጣት ሙከራ ቢያደርጉም ፖሊስ ደርሶ እንዳገታቸው ታውቋል፡፡ ሆኖም ከፖሊስ ጋር የተፈጠረ ግጭት አለመኖሩን የዩኒቨርሲቲው መምህራን ነግረውናል፡፡ ትላንት ከሰዓት በኋላ ግቢው ጭር ብሎ እንደነበር የታወቀ ሲሆን ለጥቂት ሰዓታትም ከዩኒቨርሲቲው እስከ አሜሪካ ኤምባሲ መንገድ ተዘግቶ ነበር ተብሏል፡፡

በአዲስ አድማስ

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፈደሬሽን አርማ ብሄር ብሄረሰቦችን ስለማይወክል ሊለወጥ ነው

09901688321edba926437d79e05af356_L

ጀግናው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፈደሬሽን ለረጅም ዓመታት ሲገለገልበት የቆየውን  አርማ……(ጉምበት 20 ሺህ ዘጣኝ ሞቶ የሚለው የወያኔ ቀረርቶ ትዝ አለኝ)  በቅርቡ ሊቀይረው ነው፡፡

በዛሬው ዕለት የፌደሬሽኑ የበላይ አካላት እንዳስታወቁት እና አፈ ቀላጤው ፋና ራድዮ እንዳስተጋባው ፥ ፌደሬሽኑ ሲገለገልበት የቆየው አርማ ሁሉን ስለማይወክል እና ክፍተት ስላለው ልንቀይረው ነው ብለዋል ፡፡  ለጊዜው የተሳበበው በስፖርቱ ቢኖንም ፡ ውስጥ አዋቂዎች ግን ብሄር ብህረሰቦችን ስለማይወክል በደንብ በቀለም ማሸብረቅ ስላለበት እንደሆነ ገፀዋል፡፡

አዲሱን የፌዴሬሽኑን አርማ ዲዛየን እንዲያወጣ የትግራይ ድርጅት ሀላፊነት የተሰጠው ሲሆን ከ2016 አዲሱ አመት እቅድ ከመውጣቱ በፊት እንደሚያስረክብም ታውቋል ፡፡ ቀለሙም ብዙ ቢጫ በቀይ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡

 

ሜሮን አየለ

እነ ዘላለም ወርቃገኘሁ መከላከያ ምስክሮቻቸውን አሰሙ! (አንዳርጋቸው ጽጌና እስክንድር ነጋ ለምስክርነት ተጠርተዋል)

esknderበእነ ዘላለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ የሽብርተኝነት ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት እየታየ የሚገኙት አምስት ተከሳሾች የመከላከያ ምስክሮቻቸውን አቅርበው አሰምተዋል፡፡ በዚህ መዝገብ የተካተቱት ተከሳሾችም ዘላለም ወርቃገኘሁ፣ ዮናታን ወልዴ፣ ባህሩ ደጉ፣ ሰለሞን ግርማ እና ተስፋዬ ተፈሪ ናቸው፡፡

ተከሳሾቹ ከሰኞ ህዳር 13/2008 ዓ.ም ጀምሮ በተከታታይ ለአራት ቀናት ምስክሮቻቸውን ያሰሙ ሲሆን፣ ዘላለም ወርቃገኘሁ 11 ምስክሮች፣ ዮናታን ወልዴ 5፣ ሰለሞን ግርማ 3፣ እና ባህሩ ደጉ እና ተስፋዬ ተፈሪ እያንዳንዳቸው 8 ምስክሮችን ጠርተዋል፡፡ ከእነዚህ መካከልም በአንደኛ ተከሳሽ ለምስክርነት የተጠሩት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እና ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እንዲቀርቡ አለመደረጋቸው ታውቋል፤ በተጨማሪም በእስር ቃሊቲ የሚገኙትና ለምስክርነት የተጠሩት አብርሃ ደስታ፣ የሺዋስ አሰፋ እና ዳንኤል ሺበሽን ማረሚያ ቤቱ ለተከታታይ ቀናት ከፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ቢተላለፍለትም ሳያቀርባቸው ቀርቷል፡፡
በዋናነት ተከሳሾች በማዕከላዊ ፌደራል ወንጀል ምርመራ በነበሩበት ወቅት የደረሰባቸውን አስከፊ የምርመራ ሁኔታና በዚሁ ምክንያት ተገድደው ስለሰጡት ቃል የሚመሰክሩ ምስክሮችን አሰምተዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በዚሁ በምርመራ ወቅት አብረዋቸው ታስረው የነበሩና በኋላ ላይ የአቃቤ ህግ ምስክር ሆነው ቀርበው የመሰከሩ ግለሰቦች እንዴት ተገድደው በሀሰት እንደመሰከሩባቸው ያስረዱልናል ያሏቸውን ምስክሮች አስደምጠዋል፡፡
ተከሳሾች የተከሳሽነት መከላከያ ቃላቸውን ለፍርድ ቤቱ የሰጡ ሲሆን፣ በተለይ አንደኛ ተከሳሽ ዘላለም ወርቃገኘሁ ህዳር 16/2008 ዓ.ም ለፍርድ ቤቱ በሰጠው ቃል፣ የቀረበበት ክስ ፖለቲካዊ ይዘት ያለው (politically motivated) እንደሆነና በምርመራ ወቅትም በፖሊስና ደህንነት ከተከሰሰበት ጋር በማይገናኝ መልኩ ‹‹ምርጫ 2007ን ለማደናቀፍ ቡድን አደራጅተሃል›› በሚል ሲመረመር እንደነበር አመልክቷል፡፡
ዘላለም በሰጠው ቃል የጸረ-ሽብር ህጉ አሸባሪዎችን ለመከላከልና ለመቅጣት ሳይሆን የተቃውሞ ድምጽ የሚያሰሙ ዜጎችን እና ጋዜጠኞችን ለማጥቃት እየዋለ እንደሆነም አስረድቷል፡፡ ‹‹በእኔ እምነት አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀውና ግንኙነት አለህ በሚል የተከሰስኩበት ድርጅት አሸባሪ ነው ብዬ አላምንም፡፡ ሆኖም ግን እንደ እኔ አይነቶችን ለማጥቃት መጠቀሚያ እንዲሆን ሊፈረጅ ችሏል›› ሲል ቃሉን ሰጥቷል፡፡
ለተከታታይ 41 ቀናት ቀዝቃዛና ጨለማ ክፍል በማዕከላዊ እንዳሳለፈና ለአንድ ወር ከቤተሰብ ጋር እንዳይገናኝ እንደተደረገ የተናገረው ዘላለም፣ ‹‹ለለውጥ የሚታገሉ ወጣቶች ላይ ተጽዕኖ ላለማሳደር የደረሰብኝን በደል ሁሉ እዚህ መዘርዘር አልሻም›› ሲል ገልጹዋል፡፡ በተመሳሳይ ሌሎችም ተከሳሾች በሰጡት ቃል በማዕከላዊ አስከፊ ምርመራ እንደተደረገባቸው አስረድተዋል፡፡
በዚህ መዝገብ የተካተቱት አቶ ባህሩ ደጉ እስካሁን ምስክሮቻቸውን አቅርበው ያላሰሙ ሲሆን፣ አንደኛ ተከሳሽ ዘላለም ወርቃገኘሁ እና 6ኛ ተከሳሽ ዮናታን ወልዴ ደግሞ ቀሪ ምስክሮቻቸውን የሚያሰሙ ይሆናል፡፡ ስለሆነም ዛሬ ህዳር 17/2008 ዓ.ም ‹‹ዳኞች አልተሟሉም›› በሚል ቀሪ ምስክሮችን ማሰማት ባለመቻላቸው ለህዳር 24/2008 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል፡፡
በዚሁ መዝገብ ክስ ተመስርቶባቸው የነበሩት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች የሆኑት አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ የሺዋስ አሰፋ፣ አብርሃ ደስታ እና ዳንኤል ሺበሽ እንዲሁም መምህር አብርሃም ሰለሞን በዚሁ ችሎት ነጻ መሆናቸው ቢበየንም በአቃቤ ህግ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ተጠይቆባቸው ጉዳያቸውን በእስር ላይ ሆነው እየተከታተሉ እንዳሉ ይታወቃል፡፡

 

በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር

የባለ 11% እድገታችንና ብቃት የለሽ አስተዳደር ያስከተለው ረሃብ

Meron Ayele / Norway/
ሀገራችን ላለፉት ሃያ አራትት አመታት ስለልማቷ፣ ስለእድገቷ ብዙ ተብሏል፥ እየተባለም ይገኛል። ሆኖም ግን አደገች፣ በለጸገች እየተባለ ይነገረን እንጂ ሕዝቧ/ዜጎቿ ከጊዜ ወደ ጊዜ ኑሯችን እያሽቆለቆለ፣ ፍትህ እየተዛባ፥ መብት እየተረገጠ አስከፊ ችግር ውስጥ ተዘፍቀን እንገኛለን። የሀገራችን እድገት ምስክሮች እኛውና የኛው ኑሮ መሆኑ ቀርቶ ሌሎች አውሮፓውያኖችና ለጋሽ መንግስታት ‘ለመንግስታችን’ እየመሠከሩለት፣ ወያኔም ምሥክርነታቸውን እንዳረጋገጡለት ለኛ መልሶ በቴሌቪዥንና በሬድዮ ቀንና ማታ ያደነቁረናል።
ሃገራችን ችግር ላይ ነች ብለን ስንል የታየንንና የተረዳነውን ገሃድ አውጥቶ መነጋገርና መፍትሄ መፈለግ ለህዝብና ለሃገር በማሰብ እንጂ እንደወያኔ በአግድም ወይንም የተገላቢጦሽ አተረጓጎም በሃገርና በህዝብ ላይ ችግር መፍጠር ወይንም ህዝብን ለአመጽና ለብጥብጥ ማነሳሳት ወይንም መጋበዝ ማለት አይደለም።
መንግስት ነኝ ብሎ የተቀመጠው ስብስብ የተሞላው በራስ ወዳዶች፣ ብልጣ ብልጦች፣ አስመሳዮችና የህዝብ ችግርና ሰቆቃ በማይሰማቸው ግለሰቦች ነው። ይህንን የሃገራችንን ችግር ከነችግር ፈጣሪዎቹ ልቅምቅም አድርጎ ማስወገድ የማናችንም ሃገር ወዳድ ዜጋ ሃላፊነትና ግዴታ ነው።
በነፃነት በመኖር የምንቀድማቸው ሃገራት ሰልጥነው በዴሞክራሲያዊ ስርዓትና መልካም አሰተዳደር የህዝቦቻቸውን ሰብዓዊ መብት ለማስጠበቅ ደፋ ቀና በሚሉበት በዚህ ዘመን የኋሊት የሚጓዘው ከዘመኑ ጋር መዘመን ያቃተው ወያኔ ከብዙ ዘመናት በፊት በነበረው ኢትዮጵያዊነትን የማፍረስ አስተሳሰብና የሃይል አምባገነናዊ አገዛዝ ተሸብቦ ያላስነባው ህዝብ፤ ያልጣሰው ህግና ስርዓት፤ ያላፈረሰው አንድነት፤ ያላዋረደው የህዝብ ስብዕና፤ ያልገባበት የእምነት ተቋም፤ ያልበተነው የሞያ ማህበራት፤ ያልገደለው፣ ያላሰረውና ያላስለቀሰው የህብረተሰብ ክፍል የለም::
ባለፉት አመታት በወያኔ አገዛዝ በግልጽ እንዳየነዉ የኢትዮጵያ ህዝብ እኩልነቱን፤ መብቱንና ነጻነቱን ለማስከበር የሚያደርገውን ትግል ለማኮላሸት እርስ በርሱ የሚቃረኑ ህጎችና መመርያዎችን አርቅቆ እያጸደቀ ሠላማዊ ዜጎችን አስሯል፤ አንገላቷል፤ ገድሏል፤ ለማምለጥ የታደሉትንም ከአገር በግፍ እንዲሰደዱ አድርጓል።
በአሁኑ ወቅት በሃገራችን በኢትዮጵያ ተንሰራፍቶ ለሚገኘው ረሃብና ድርቅ ዋና መንስዔዎች የተፈጥሮ አየር መዛባት ብቻ ሳይሆን በዋናነት የመልካም አስተዳደር እጦት ነው፡፡ የችግሩ መንስዔ አንኳር ችግር በየደረጃው የሚገኘው የመንግስት አካላት ሃገርንና ህዝብን በሰለጠነ መንገድ ለማስተዳደር ብቃት የለሽነት እና ብልሹ አስተዳደር እንጂ ባለስልጣናቱ እንደሚደሰኩሩት አካባቢያዊ ነገሮች አይደሉም፡፡
በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ እስከዛሬ እየተከሰተ ያለው ረሃብ ከተፈጥሯዊነቱ ይልቅ ሰው ሰራሽነቱ ነው የሚያመዝነው፡፡ ይህም ማለት ለረሃቡ መንስዔ ሙስና፣ ብልሹ አስተዳደር፣ የሙያ እና የአስተዳደር ብቃት የለሽነት እና በአሁኑ ጊዜ በሀገሪቱ ላይ ተንሰራፍቶ የሚገኘውን ችግር ለማስወገድ የሚያስችል የፖለቲካ ፈቃደኝነት እና ፍላጎት የሌለው አምባገነን እና ጨካኝ ዘረኛ መንግስት በስልጣን እርካብ ላይ ተፈናጥጦ የመገኘቱ ሁኔታ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ በስልጣን እርካብ ላይ ተንጠልጥለው የሚገኙት ቡድኖች ትክክለኛ ለሆነ ዕቅድ እና ለህዝቦች ደህንነት ጠቀሜታ ያላቸውን ፖሊሲዎች ለመንደፍ የማይችሉ፣ ህዝብን በዘርና በቋንቋ በማበጣበጥ እድሜያቸውን ለማራዘም የሚፈልጉ ጠባቦች፣ ሀሳበ ግትር እና ለተሻለ ለውጥ በምንም ዓይነት መልኩ ዝግጁ ያልሆኑ የጫካ ወሮበላ የአስተሳሰብ አድማስን የተላበሱ ፍጡሮች ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ ሃገራችን ሀሳብን በነፃነት ያለፍርሀት መግለፅ የማይቻልባት፤ የዜጎች የኑሮ ደረጃ ከዕለት ዕለት እየተባባስ የሚሄድባት፤ ዘመናዊ የመረጃ መገናኛዎች ሆን ተብለው የታገዱባት፤ የህዝቦቿን ጥንታዊና ብርቅዬ የሆነውን መከባበርና አንድነት በዘር ጥላቻና በሀይማኖት ለመከፋፈል አገዛዙ የሚጥርበት፤ ዜጎች አለአግባብ የሚታሰሩባት፣ የሚገደሉባት፤ ዜጎች በከፍተኛ ሁኔታ የሚሰደዱባት፤ ነፃ፣ ፍትሐዊና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ያልተካሄድባት፤ ዜጎች ከመኖሪያቸውና ከቀዬአቸው የሚፈናቀሉባት፤ ለሕግ ተገዢ ያልሆነ መንግሥት ያለባት፤ ዜጎች የገዢው ፓርቲ አባል ካልሆኑ በስተቀር በነፃነት ሠርተው መኖር የማይችሉባት፤ ነፃ ሚዲያ የሌለባት፤ ዜጎች ለሀብት ንብረታቸው ዋስትና የማያገኙባት፤ ህዝባዊ መንግሥት የሚናፍቅ ህዝብ ያለባት፤ በሀገሪቱ የሚገኙ ሁሉም ተቋማት የገዢው ፓርቲ ፖለቲካዊ መጠቀሚያ የሆኑባት፤ ቤቶች በቁመታቸው ማደጋቸው እንደዕድገት የሚቆጠርባት ሀገር ሆናለች። ስለሆነም ኢትዮጵያንና ህዝቧን ለመታደግ በየትኛውም የትግል መስክ ተሳትፎ በማድረግ ለነፃነት፣ ለፍትህ እና ለእኩልነት በሚደረገው ትግል ውስጥ የየራሳችንን አሻራ ለማሳረፍ ለተግባራዊ ትግል እንትጋ፡፡
ስለዚህ ኢትዮጵያውያን የአንድነት ሃይሎች በመተባበር፣ በመጣመርና በመዋሃድ ሃይልን፣ እውቀትን፣ ህብረትን እንዲሁም ገንዘብን በማቀናጀት የወያኔን አገዛዝ ከኢትዮጵያ ምድር ወደ ከርሰ መቃብር ለአንዴና ለመጨረሻ አሸቀንጥሮ ወርውሮ ሃገርንና ህዝብን ለነጻነት ለማብቃት በጋራ መታገል ግዴታችን መሆኑን አውቀን በአንድነት ስርዓቱን ማስወገድ ማንኛውም ሃገሬንና ህዝቤን እወዳለሁ የሚል ዜጋ ሊነሳለት እና ሊተገብረው የሚገባ መሆኑን በመግለጽ የበኩሌን ሃሳብ ለማቅረብ እወዳለሁ::